ችግሮቻችንን ሁሉ ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ የውስጥ ጉዳዮቻችንን በማየት ማስተካከል ላይ ማተኮር ያስፈልጋል
“ችግሮቻችንን ሁሉ ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ የውስጥ ጉዳዮቻችንን በማየት ማስተካከል ላይ ማተኮር ያስፈልጋል” … አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ
“ችግሮቻችንን ሁሉ ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ የውስጥ ጉዳዮቻችንን በማየት ማስተካከል ላይ ማተኮር አለብን” ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናገረ።
በሩጫው የበርካታ የዓለም ሪከርዶች ባለቤትና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበቡትን ጫናዎች አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ኢትዮጵያ በዘመናት የተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ያለፈች ቢሆንም፤ አሁን የሚታየው ጫና የመጣው “በህዳሴ ግድቡ ግንባታና በድህነታችን ምክንያት ነው” በማለት ነው የገለጸው።
ከኢትዮጵያ ይልቅ ያደጉት አገሮች አቻቸውን ለመፈለግ በሚያደርጉት ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያን እየተጫኗት መሆኑንም በመጥቀስ፤ ለዚህም አንዱ ማሳያ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የድህነት ደረጃ አንጻር አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ሲገባት፤ ከግብጽ ጎን መቆምን ትመርጣለች ይላል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዘርፍ ያገኘችውን ተሰሚነት ያነሳው አትሌት ኃይሌ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የአትሌቲክስ ውድድር መርሃ ግብሮችን እስከማስቀየር የሚደርስ ተሰሚነት አላት ብሏል።
በአውሮፓውያኑ ዘመን ቀመር በ1999 በጃፓን የተካሄደውን የውድድር መርሃ ግብር ማስቀየሩን በማስታወስ ኢትዮጵያ በዘርፉ ክብርና ተሰሚነት ማትረፏን ገልጿል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ባስመዘገበችው ውጤት ከፍ ያለችውን ያክል በኢኮኖሚው መስክም መድገም አለባትም ብሏል።
የኢትዮጵያን ስኬት እውን ለማድረግም “ችግሮቻችንን ሁሉ ውጫዊ ከማድረግ ይልቅ የውስጥ ጉዳዮቻችንን በማየት ማስተካከል ላይ ማተኮር አለብን”በማለትም ገልጿል።
”ምንም ይሁን ምን አሁን ይህ ሁሉ ጫና የሚደርስብን ባለማደጋችንና ባለመለወጣችን መሆኑን ሁሉም ማወቅ አለበት” ብሏል አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ።
አሁን ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመለወጥ በተለይም ከወጣቱና ከባለሃብቱ ብዙ ሥራ ይጠበቃል ነው ያለው።
“ወጣቱ አገር ወዳድና ስራ ፈጣሪ፤ ባለሃብቱም ከልማት አጋርነትና ስራ ፈጣሪነቱ በተጨማሪ በታማኝነትና በቅንነት ለአገሩ መስራት አለበት” ሲል መልእክት አስተላልፏል።
“ሁላችንም በጋራ ቆመን ይህንን ካደረግን የትኛውም ማዕቀብ፣ የትኛውም ክልከላ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን አያሳስብም በማለትም ገልጿል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ለኢትዮጵያ ይጠቅማሉ ባላቸው የሥራ ዘርፎች ተሰማርቶ ለ3 ሺህ 500 ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር አገሩን እያገዘ መሆኑን አንስቷል።
በሆቴል ኢንቨስትመንት፣ የኤሌክትሮኒክስ መኪኖችን በመገጣጠም፣ በግብርና ዘርፍና በሪል ስቴት እንዲሁም በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
”ሁሉም በሚችለው ሁሉ አገርን በሚያሳድግና በሚለውጡ ተግባራት ላይ ቢያተኩር ኢትዮጵያ ታድጋለች፣ ትለወጣለች” ሲልም መልእክቱን አስተላልፏል።
በኢትዮጵያ ላይ ሰሞኑን እየተስተዋለ ባለው ያልተገባ ጫና የተቆጨን ሁሉ እድገትና ለውጥ ለማምጣት በጋራ መቆም አለብን በማለትም ጥሪ አስተላልፏል።