ታላቅነት ትልቅነትን ይፈጥራል እንጂ ትልቅነት ታላቅነት አይፈጥርም።
ታላቅነት ትልቅነትን ይፈጥራል እንጂ ትልቅነት ታላቅነት አይፈጥርም። ግሪክና ሮም ዓለምን የቀረጹት በትልቅነታችው ሳይሆን በታላቅነታቸው መሆኑን መርሳት የለብንም። በእንግሊዝ ግዛት ፀሐይ አትጠልቅም የተባለው እንግሊዝ ትልቅ ሆና ሳይሆን በጊዜው ታላላቅ እንግሊዛውያን በአንድም በሌላም መንገድ በፈጠሩት የታላቅነት ማንነት ነው። ስፔንና ኦቶማን ቱርክ በአንድ ወቅት ዓለምን ያንቀጠቀጡት በትልቅነት አይደለም።
ስለዚህ ትልቅነት ሊያመጻድቀን ትንሽነትም ሊያሸማቅቀን አይገባም። ጥረታችን በታላላቅ ኢትዮጵያውያን በኩል የኢትዮጵያን ታላቅነት መፍጠር ነው። ታላቅነታችንን የምንፈጥረው ደግሞ በታላላቅ ሐሳቦች የታነጹ ታላላቅ ዜጎችንና መሪዎችን በመፍጠር ነው። ታላቅ ሀገር የሚኖረን ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ታላላቅና ጽኑ ተቋማትንና ድንበር ዘለል ዓለም አቀፍ አስተሳሰብና ባህልን መፍጠር ስንችል ነው። ታላቅነት የሚፈጠረው በመደመር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት ላይ ተመሥርተን ታላላቅ ሥራዎችን በጋራ መሥራት ስንችል ነው።