በትግራይ ክልል በተቀናጀ ሁኔታ ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበ ነው!

በትግራይ ክልል በተቀናጀ ሁኔታ ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጅታል ሚዲያ ኃላፊ ወይዘሮ ቢልለኔ ስዩም አስታወቁ።ወይዘሮ ቢልለኔ በትግራይ ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ፣ እስካሁን ሶስት ዙር የምግብ ድጋፍ ተደርጓል።
በመጀመሪያው ዙር ለአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ፣በሁለተኛውና በሶስተኛው ዙር ለአራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር ከተደረገው ድጋፍ ሰባ በመቶ የሸፈነው ፌዴራል መንግሥት መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ ቢልለኔ፣ ሰላሳ በመቶ መንግሥታዊ ባልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች መሸፈኑን አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት ድጋፉ እየተደረገላቸው ካሉት ዘጠና ሁለት ወረዳዎች ሰባ ዘጠኙ መንግሥታዊ ባልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ አሥራ ሶስቱ በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
የሰብአዊ ድጋፍ ቁሳቁሶችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግም በመቀሌ የማስተባበሪያ ማእከል ተቋቁሟል። ማእከሉ ምግብ ነክና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎችን በተቀናጀ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ የሚጠቅም ነው። ይህም በአራት ደረጃ በክልል፣ በዞን፤ በወረዳና በምግብ ማደያ ጣቢያዎች እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል። ይህም ሆኖ የተጀመረውን ድጋፍ በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ በአንዳንድ ቦታዎች የጸጥታ ችግር የቁሳቁስና የገንዘብ እጥረት እንዲሁም የተዛቡ መረጃዎች መውጣት መሰናክል መሆናቸውን አመልክተዋል።
Via : የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጅታል ሚድያ ኃላፊ