መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ጠንካራ እምቅ አቅም ተገንብቷል

ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ
በመከላከያ የሠራዊት ውስጥ ጠንካራ አቅም መገንባቱን የመከላከያ የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ አስታወቁ።
በመከላከያ ሠራዊት በኅብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ የአዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ በቀረበው የPSC ፕሮግራም የካሪኩለም ክለሳ ወርክሾፕ ተካሂዷል።
የካሪኩለም ክለሳው የምድር ኃይልን፣ የአየር ኃይልን፣ የባህር ኃይልን እና የሳይበር ደህንነት ስትራቴጂክ አመራርን አቅም እንደሚያሳድግ ተመልክቷል።
የካሪኩለም ክለሳው ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው የማበልጸጊያ ሐሳብ እና የሥራ መመሪያ የሰጡት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ፣ ለውጥ የሚያመጡ እና ብቃትን የሚጨምሩ መሰል ሥራዎች ሊበረታቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከሁሉም በላይ ካሪኩለሙ በራስ አቅም የተሠራ መሆኑ ምን ያህል ጠንካራ አቅም በሠራዊታችን ውስጥ እንዳለ የሚያመለክት ነው ብለዋል።
የትምህርት እና ሥልጠና ሪፎርሙ ከታችኛው አመራር እስከ ከፍተኛ አመራሩ ድረስ በትኩረት እና በክትትል ይሠራበታልም ብለዋል።
ወርክሾፑን የመሩት የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜ/ጄ ይልማ መርዳሳ፣ የካሪኩለም ክለሳው የአየር ኃይልን፣ የምድር ኃይልን፣ የባህር ኃይልን እና የሳይበር ደህንነትን ስትራቴጂክ አመራርን አቅም በሚያሳድግ መልኩ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ ከሀገራችን አልፎ በአፍሪካ ከሚገኙ ጆይንት ስታፍ ኮሌጆች ጋር ተወዳዳሪ እና ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።